Abstract:
የዚህ ጥናት አላማ በ2006ዓ.ም ታትሞ ስራ ላይ በዋለው የ7ኛ ክፍል አማርኛ እንደአፍ
መፍቻ ቋንቋ የቃላት ትምህርት አተገባበር በሁለት ት/ቤቶች መፈተሽ ነው፡፡ በዚህ
ፍተሻም መምህራን የቃላት ትምህርት ይዘቶችን እንዴት ተገበሯቸው? ዘዴዎችን በአግባቡ
እንዳይተገበሩ ወይም እንዳያቀርቡ የሚያደርጉ ተላውጦዎች የትኞቹ ናቸው? ለሚሉ
ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ተሞክሯል፡፡ ጥያቄዎቹንም ለመመለስ መረጃዎች ከሁለቱም
ትምህርት ቤቶች በክፍል ውስጥ ምልከታ፣ በቃለ መጠይቅና በጽሑፍ መጠይቅ
ከመምህራንና ከተማሪዎች ተሰብስቧል፡፡ ጥናቱ ትኩረት ያደረገባቸው ትምህርት ቤቶችና
መምህራን በአመች ናሙና አመራረጥ ዘዴ የተመረጡ ሲሆን የተማሪዎች አመራረጥ ደግሞ
ከእድል ሰጭ ንሙና አመራረጥ ዘዴ ውስጥ በረድፋዊ ንሙና አመራረጥ ዘዴ ከሁለቱም
ትምህርት ቤቶች ተመርጠው የጽሑፍ መጠይቁን እንዲሞሉ ተደርገዋል፡፡ በእነዚህ ሶስት
የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች የተሰበሰበው መረጃ ትንተና በአይነታዊና በመጠናዊ ዘዴ
ከተካሄደ በኋላ ከጥናቱ ውጤት ለማረጋገጥ እንደተቻለው መምህራን በክፍል ውስጥ የቃላት
ትምህርት አተገባበራቸው ወይም አቀራረባቸው በተሻለ ደረጃ ላይ መሆኑን በጥናቱ
ተደርሶበታል፡፡ ይሁን እንጅ ትኩረት ያልሰጧቸውም እንዳሉ ለማየት ተችልሏል፡፡
ለአብነትም ስዕሎችን፣ ቻርቶችንና ምስሎችን በመጠቀም ቃላትን ማቅረብ ክፍተት
የታየባቸው ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የቃላት ትምህርት በክፍል ውስጥ በአግባቡ
እንዳይቀርቡ የሚያደርጉ ተላውጦዎች እንዳሉም በጥናቱ ተደርሶበታል፡፡ እነዚህም ከኮቪድ
19 አኳያ፣ ከማስተማሪያ መሳሪያዎች አኳያ፣ ከመምህራን አንጻር፣ ከተማሪዎች አንጻር፣
ከትምህርት ቤቱ አቀማመጥ አንጻር እንዲሆኑ ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ በመጨረሻም በቃላት
ትምህርት መማር ማስተማር ሂደት ውስጥ የሚታዩትን ጉልህ ችግሮች ተለይተው ቀጣይ
የሚሻሻሉበትንና ችግሮቹ የሚቀረፉበትን የመፍትሄ ሃሳቦች ጠቆም ለማድረግ ተሞክሯል፡