Abstract:
ይህ ጥናት ዋነኛ ዓላማ አድርጎ የተነሳው የሂደት ተኮር የቋንቋ ማስተማር ዘዴ የተማሪዎችን
የመጻፍ ክሂል ችሎታ እና ግለብቃት ከማሻሻል አንጻር ያለውን ተጽዕኖ ለመፈተሽ ነው፡፡
ጥናቱም ከፊል ሙከራዊ ሲሆን፣ የተካሄደውም በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን
በሚገኘው የአይከል አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በትምህርት
ቤቱ ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል የአስረኛ ክፍል ተማሪዎች በአመቺ የናሙና ስልት ከተመረጡ
በኋላ፣ በተራ ዕጣ የናሙና አመራረጥ ስልት በአንድ መምህር የሚማሩ ሁለት ምድብ
ተማሪዎች ተለይተው በቅድመ ፈተናው ሂደት ተሳትፈዋል፡፡ ከሁለቱ ምድቦች መካከል በቅድመ
የመጻፍ ክሂል ፈተና ተቀራራቢ አማካይ ውጤቶች ያስመዘገቡ ሁለት ምድቦች ከተለዩ በኋላ
በተራ የዕጣ ናሙና ስልት አንዱ የሙከራ ሌላኛው የቁጥጥር ቡድን ሆኖ በጥናቱ ውስጥ
እንዲሳተፍ ተደርጓል፡፡ በመረጃ መስብሰቢያ ዘዴነት ፈተና እና የጽሑፍ መጠይቅ ሥራ ላይ
ውለዋል፡፡ ፈተናው፣ ቅድመ እና ድኅረ ፈተናን ያካተተ ነው፡፡ ቅድመ ፈተናው የተሰጠበት
ዓላማ ተማሪዎች ከሙከራ ጥናቱ በፊት ያላቸውን የመጻፍ ክሂል ውጤት ተቀራራቢ መሆን -
አለመሆኑን ለመፈተሽ ሲባል ነው፡፡ የድኅረ ፈተናው ዓላማ ደግሞ የሙከራ እና የቁጥጥር
ቡድን ሆነው የተመረጡት ተማሪዎች በተለያዩ የማስተማሪያ ዘዴዎች የመጻፍ ክሂልን ከተማሩ
በኋላ በመካከላቸው ጉልህ ልዩነት መኖር- አለመኖሩን ለመፈተሽ ነው፡፡ በሌላ በኩል የጽሑፍ
መጠይቅ የተማሪዎቹን የመጻፍ ግለብቃት ለመለካት የቀረበ ነው፡፡ ተተኳሪ የሆኑት ተማሪዎች
ከመጻፍ ልምምዱ በፊት (ቅድመ ጽሑፍ መጠይቅ) እና በኋላ (ድኅረ የጽሑፍ መጠይቅ)
እንዲሞሉ ተደርጓል፡፡ በቅድመ ፈተና እና በቅድመ የጽሑፍ መጠይቅ የተገኙ ውጤቶች
በዳግም ናሙና ቲ- ቴስት ትንተና ዘዴ እንዲሁም በድኅረ ፈተና እና በድኅረ የጽሑፍ መጠይቅ
የተገኙ ውጤቶች በባዕድ ናሙና ቲ ቴስት ትንተና ዘዴ እንዲሰሉ ተደርጓል፡፡ የተገኙት
ውጤቶች እንደሚያመለክቱት በቅድመ ፈተና እና በቅድመ የጽሑፍ መጠይቅ ተመጣጣኝ
አማካይ ውጤቶች የተመዘገበባቸው ቡድኖች፣ በድኅረ ፈተና ይዘት፣ አደረጃጀት፣ ቃላት፣
የቋንቋ አጠቃቀም እና ሥርዓተ አጻጻፍ እና በድኅረ የጽሑፍ መጠይቅ ግለ ብቃት የሙከራ
ቡድኑ ተማሪዎች ከቁጥጥር ቡድኑ ተማሪዎች ጉልህ የሆነ ልዩነት አሳይተዋል (P= <0.05)::
ይህም ውጤት የሒደት ተኮር የቋንቋ ማስተማር ዘዴ የተማሪዎችን የመጻፍ ክሂል ችሎታን
እና ግለብቃትን ከማሻሻል አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ሊጠቁም ችሏል፡፡ ከመጻፍ ክሂል
ችሎታ እና ግለብቃት አንጻር የተገኙት ውጤቶች ላይ በመመስረት ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው
ከተደረገ በኋላ፣ የሂደታዊ ዘዴ የመፃፍ ትምህርት አቀራረብ የተማሪዎችን የመፃፍ ክሂል
ለማዳበር ጥሩ አስተዋፅዖ ያለው መሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ከአተገባበር አኳያ
የተማሪዎችን የመማር ሂደት ካለገደበ መተግበር ስላለበት መምህራን ከአተገባበር አኳያ
የተማሪዎችን የመማር ሁኔታ ሊያጤኑት ይገባል፡፡ መምህራን የሂደታዊ አቀራረብን በክፍል
ውስጥ ሲተገብሩ የሚጠበቀው ትምህርታዊና ማህበራዊ ስኬት እንዲመጣ ተማሪዎች አዲሱን
አቀራረብ በሚገባ እንዲረዱት እና በትምህርቱ ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፉ በቂ ክትትልና ድጋፍ
ሊያደርጉ ይገባል፡፡ መምህራን ጥሩ ግንዛቤ ኖሯቸው በክፍል ውስጥ በተገቢው ሁኔታ
መተግበር እንዲችሉ የሚያደርጋቸው በቂ ስልጠና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የመፍትሄ
ሀሳቦች እና የጥናት ጥቆማዎች እንዲቀርቡ ተደርጓል፡