Abstract:
የዚህ ጥናት ዋነኛ አላማ አድርጎ የተነሳዉ ሰዋስውን በቀጥተኛና ኢ-ቀጥተኛ ዘዴዎች ማስተማር የተማሪዎችን
የሰዋስው እውቀትና ሰዋስውን የመማር ተነሳሽነት በማጎልበት ረገድ ያለውን ሚና መፈተሸ ነው፡፡ በመሆኑም
ጥናቱ ከፊል ፍትነታዊ ስልት ተከትሏል፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች በአማራ ክልል በምዕራብ ጐጃም ዞን በደቡብ
አቸፈር ወረዳ በሚገኘው ላሊበላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት በ9ኛ ሴክሽን በ2013 ዓ.ም
ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ በነበሩ ተማሪዎች ውስጥ በእድል ሰጭ የናሙና ዘዴ የተመረጡ 78 ተማሪዎች
ናቸው፡፡ የተመረጡት ክፍሎች ”A” እና ”E” ተማሪዎች ሲሆኑ ከነዚህ ሁለት ክፍሎች የጥናቱ ተሳታፊዎች
በቀላል እጣ የናሙና ዘዴ በሁለት ቡድን ተከፍለው አንደኛው የቀጥተኛ ዘዴ ቡድን እና ሁለተኛው የ ኢ ቀጥተኛ ዘዴ ቡድን በማድረግ በጥናቱ ውስጥ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡በመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴነት ፈተና እና
የጽሁፍ መጠይቅ ስራ ላይ ውለዋል፡፡ለእያንዳንዱ ቡድን ለአራት ሳምንት (ለስምንት ክፍለ ጊዜ) የቃል ክፍሎችና
የአረፍተ ነገር ምንነትና ተዋቃሪዎች ላይ ያተኮረ የሰዋስው የትምህርት ይዘት ተሰጥቷል፡፡ ተማሪዎች ትምህርቱን
ከመማራቸው በፊትና ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኃላ በአጥኝው ፈተና ተሰጥቷል፡፡ በፈተናዎች የተሰበሰበው
መረጃ ሲታይ በቅድመ ፈተና ወቅት የቀጥተኛ ዘዴ ቡድኑ እና የኢ-ቀጥተኛ ዘዴ ቡድኑ ተማሪዎች አማካይ
ውጤት በቲ-ቴስት ቀመር ተሰልቶ በተገኘው ውጤት መሰረት ጉልህ ልዩነት እንደሌላቸው አሳይተዋል፡፡በሌላ
በኩል በድህረ ፈተና ወቅት የኢ-ቀጥተኛ ዘዴ ቡድኑ ከቀጥተኛ ዘዴ ቡድኑ ተጠኝዎች አማካኝ ውጤት ልዩነት
ታይቶበታል፡፡ በተጨማሪም የጽሑፍ መጠይቅ በሊንከርት ስኬል ለመረጃ መሰብሰቢያነት ጥቅም ላይ
ውሏል፡፡በጽሑፉ መጤይቅ በድግግሞሽና በመቶኛ በተሰበሰበው መረጃ እንደታየው ሰዋስውን የመማር ተነሳሽነትን
በማጎልበት ረገድ የሙከራ ጥናቱ ከመካሄዱ በፊት የጥናቱ ተተኳሪዎች የመማር ተነሳሽነታቸው አዎንታዊ ሆኖ
ተገኝቷል፡፡በዚህ ጥናት የታየው ግኝት በኢ-ቀጥተኛ ዘዴ የተማሩ ተማሪዎች በቀጥተኛ ዘዴ ከተማሩት ጋር
ሲነጻጸር የሰዋስው እውቀታቸው የተሻለ ሆኗል፡፡ ይህም የሚያሳየው ተማሪዎች ሰዋሰውን በኢ-ቀጥተኛ ዘዴ
የተማሩ በተማሪዎች የሰዋሰው እውቀት መዳበር ያለውን ሚና የጎላ ያደርገዋል፡