Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና አላማ በ2004 ዓ.ም በአንደኛ እትም ታትመው በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ያሉትን የአስረኛ
ክፍል የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መፃሕፍት እና መርሀ ትምህርቱ ያላቸውን ዝምድና በመፈተሽ ላይ ያተኮረ
ነው፡፡ የጥናቱን ዋና አላማ ከግብ ለማድረስ አጥኚው በሰነድ ፍተሻ በአስረኛ ክፍል በአማርኛ ቋንቋ
መማሪያ መፃሕፍት እና በመርሃ ትምህርቱ መካከል ያለውን የክሂልና የእውቀት ዘርፎች የይዘት አደረጃጀት
እና ለምዘና ተግባር የዋሉ ስራዎችን በአይነታዊ እና መጠናዊ ዘዴዎች ተንትኖ አቀርቧል፡፡ ይህን ዓላማ
ከግብ ለማድረስ ተዛምዷዊ የምርምር ንድፍ ተግባራዊ ሁኗል፡፡ እንዲሁም አላማ ተኮር የናሙና ዘዴን
በመከተል በአስረኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መፃሕፍትእና በመርሀ ትምህርቱ ላይ አተኩሯል፡፡
በሰነድ ፍተሻ አማካኝነት ከናሙናው የተሰበሰበው መረጃ ተደራጅቶ በፒርሰን ፕሮዳክት ሞመንት
የተዝምዶ መለኪያ በመጠቀም ተተንትኗል፡፡በጥናቱ ውጤት መሰረት የአስረኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ
መማሪያ መፃህፍት ከመርሃ ትምህርቱ ጋር የይዘት ተከታታይነት ዝምድና እንዳለው ታይቷል፡፡
በመማሪያ መፅሃፉም ይሁን በመርሐ ትምህርቱ የተለያዩ ምዕራፎች ላይ የቀረቡ ይዘቶች የተማሪዎችን
የመማር ሁኔታ ወይም ዳራዊ እውቀት ጠብቀው የቀረቡ ናቸው፡፡ መማሪያ መፃህፍቱ ከመርሐ ትምህርቱ
ጋር ያለው የይዘት ተከታታይነት የዝምድና መጠን በስታትስቲክስ ትንተናው 0.98 በመሆኑ በአዎንታዊ
አቅጣጫ በጣም ከፍተኛ የተዛምዶ መጠን እንዳለው ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ ይሁን እንጅ በመርሐ ትምህርቱ
በሁሉም ምዕራፎች የቀረበው፣ ዝርዝር ሃሳብ መለየት በመማሪያ መፃሕፍቱ ምዕራፍ ሁለት እና ሦስት
አልተካተተም፡፡ በመቀጠልም በአስረኛ ክፍል በአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መፃህፍትና በመርሃ ትምህርቱ
የይዘት ተለጣጣቂነት ተዛምዶ መመርመር ነበር፡፡ መማሪያ መፃህፍት ከመርሃ ትምህርቱ ጋር ያለው
የክሂልና የእውቀት ዘርፎች የይዘት ተለጣጣቂነት የዝምድና መጠን በስታትስቲክስ ትንተናው 0.91
በመሆኑ በአዎንታዊ አቅጣጫ በጣም ከፍተኛ የተዛምዶ መጠን እንዳለው ውጤቱ አሳይቷል፡፡ እንዲሁም
በአስረኛ ክፍል በአማርኛእና እንግሊዝኛ ቋንቋ መማሪያ መፃህፍት መካከል ያለው የክሂሎችና የእውቀት
ዘርፎች የይዘት ውህዳዊነት ተዛምዶ የተመረመረ ሲሆን የዝምድና መጠኑ በስታትስቲክስ ትንተናው
0.84 በመሆኑ በአዎንታዊ አቅጣጫ በጣም ከፍተኛ የዝምድና መጠን እንዳለው ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ የዚህ
ጥናት የመጨረሻው ጉዳይ በአስረኛ ክፍል በአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መፃሕፍትና በመርሃ ትምህርቱ
ውስጥ ለምዘና ተግባር የዋሉ ስራዎች ያላቸውን ዝምድና መፈተሸ ሲሆን በዚሁ መማሪያ መፃሕፍት እና
በመርሃ ትምህርቱ ውስጥ ለምዘና ተግባር የዋሉ ስራዎች የዝምድና መጠን በስታትስቲክስ ትንተናው
0.99 በመሆኑ በአዎንታዊ አቅጣጫ በጣም ከፍተኛ የተዛምዶ መጠን እንዳለው ውጤቱ አሳይቷል፡፡
በጥናቱ ግኝት ላይ በመመስረት የመፍትሄ ሓሳቦች የተጠቆሙ ሲሆን መፃሕፍት አዘጋጆች በቀጣይ የቋንቋ
መማሪያ መፃሕፍት ሲያዘጋጁ ሙሉ በሙሉ ከመርሐ ትምህርቱ ጋር ዝምድና እንዲኖረው ይጠበቃል፡፡